የሀገር ውስጥ ዜና

ሀገራዊ የፋይናንስ አቅም የዋጋ ንረትን ሊያረጋጋ በሚችልና የስራ እድልን በሚፈጥሩ ዘርፎች ላይ ማዋል እንደሚገባ ተመላከተ

By Amele Demsew

November 07, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር ውስጥ ያለውን ውስን ፋይናንስና የኢንቨስትመንት አቅም የዋጋ ንረትን ሊያረጋጋ በሚችል፣ የስራ እድልን በሚፈጥሩና የውጭ ምንዛሬን ሊያስገኙ በሚችሉ ዘርፎች ላይ ማዋል እንደሚገባ ተመላከተ።

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ የነበራቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቡሌ መሃሪ (ዶ/ር) እንደገለጹት÷ በኢኮኖሚው ውስጥ ባለው የዋጋ ንረት ምክንያት ሰዎች ገንዘባቸውን በባንክ ከማስቀመጥ ወይም በማምረት ላይ ከማዋል ይልቅ ሌሎች አማራጮችን ሲጠቀሙ ይታያሉ፡፡

የሀገሪቱ የመዕዋለ ንዋይ አቅም በቀዳሚነት የዋጋ ግሽበትን በሚያረጋጉ ዘርፎች ላይ ሊውል እንደሚገባም ገልጸዋል።

ባለሃብቶች ገንዘባቸውን ባንክ በማስገባት የሚያገኙት ትርፍ እጅግ አናሳ ከመሆኑና የዋጋ ግሽበቱ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ገንዘባቸውን ከባንክ በማሸሽ እሴት በማይጨምሩ ጉዳዮች ላይ ለማዋል እንደሚገደዱ ጠቁመዋል።

በመሆኑም ገንዘባቸውን ቋሚ ንብረት በሆኑ እንደ መኪና፣ ቤትና የመሳሰሉት ላይ በማዋል ይህንኑ በማገለባበጥ ትርፍ ማግኘትን ምርጫቸው እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

በዚህም የተነሳ ባንኮች የገንዘብ እጥረት ስለገጠማቸው ለማበደር መቸገራቸውን ገልጸው፤ ኢኮኖሚውን ትርጉም ባለው መልኩ ሊያግዙ የሚችሉ የግብርናና የአምራች ዘርፎች ተገቢውን የፋይናንስ ድጋፍ የማያገኙበት ሁኔታ እንደሚፈጠር አንስተዋል።

ይህም የግብርናውና የአምራቹ ዘርፍ አቅም በማሳጣት ወደ ገበያ የሚቀርብ ምርት እንዳይኖር በማድረግ ግሽበቱን በከፍተኛ ደረጃ ያባብሰዋል ይላሉ ፡፡

ስለሆነም በሀገር ውስጥ ያለውን ውስን ፋይናንስና የኢንቨስትመንት አቅም የዋጋ ንረትን ሊያረጋጋ በሚችል፣ የስራ እድልን በሚፈጥሩና የውጭ ምንዛሬን ሊያስገኙ በሚችሉ ዘርፎች ላይ ማዋል እያጋጠሙ ያሉ የኢኮኖሚ ፈተናዎችን ለመሻገር እንደሚያስችል መክረዋል።

የባንኮችን የወለድ ምጣኔ ካለው የዋጋ ንረት ጋር በማነጻጸር በወለድ ምጣኔ ላይ ማስተካያ ማድረግና የፋይናነንስ አሰራሩን ለኢኮኖሚው በሚጠቅም መልኩ የተቃኘ ማድረግን በመፍትሄነት አመላክተዋል።

የዋጋ ግሽበቱን የሚያባብሱ አሰራሮች ላይም ከፍተኛ ቁጥጥር ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡