የሀገር ውስጥ ዜና

ከ343 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ

By Mikias Ayele

November 06, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ343 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዙን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ ከጥቅምት 16 እስከ 22 ቀን 2016 ዓ.ም  በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ባደረገው ክትትል ነው እቃዎቹ የተያዙት፡፡

በዚህም 223 ሚሊየን ብር የገቢ የኮንትሮባንድ እቃዎች እና 120 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የወጪ በድምሩ 343 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዛቸው ተገልጿል፡፡

ከተያዙት እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሃኒት፣ ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ እቃዎች የጦር መሳሪያዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣የምግብ ዘይት እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በበረራና በጥቆማ እንደተያዙ የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡