Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአእምሮ ጤንነት የሚለካው በጤናማ ማህበራዊና ግለሰባዊ መስተጋብር ነው – ዶ/ር ያሬድ ዘነበ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአንድ ሰው አእምሮ ጤናማነት የሚለካው በሚያደርገው ማህበራዊና ግለሰባዊ መስተጋብር መሆኑን የነርቭ ሃኪም ዶ/ር ያሬድ ዘነበ አመላክተዋል፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የአእምሮ ጤናን አስመልከቶ የነርቭ ሃኪም ከሆኑት ዶ/ር ያሬድ ዘነበ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ዶ/ር ያሬድ እንደሚሉት፤ የአዕምሮ ጤንነት ማለት የነርቭ ስርዓት ጤንነት ማለት ነው፡፡

ብዙ ጊዜ አዕምሮንና አንጎልን የተለያየ አካላት አድርገን እናያለን ያሉት ባለሙያው፤ ነገር ግን አንጎል ከሚዳሰሰው የራስ ቅላችን ውስጥ ያለው ሲሆን የሚሰራው ተግባር ደግሞ አዕምሮ ወይም የአዕምሮ ስራ እንደሚባል ይገልጻሉ፡፡

አንድ ሰው አዕምሮው ጤናማ ነው የምንለውም አዕምሮውን ተጠቅሞ ማበራዊ ግለሰባዊና አካባቢያዊ ፍላጎቱን አሟልቶና መስተጋብር ፈጥሮ ጤናማ ሆኖ መኖር ሲችል ብቻ ነው ይላሉ፡፡

የአዕምሮ ጤና ችግር ከተወለድን ጀምሮ እስከ ህይዎታችን መጨረሻ ድረስ ሊያጋጥም ይችላል የሚሉት ባለሙያው፤ አንዳንዶቹ የአዕምሮ ጤና ችግሮች ከአፈጣጠርና ከአወላለድ ሂደት ጋርም ሊከሰቱ እንደሚችሉ ይናገራሉ፡፡

የአዕምሮ እድገት ውስንነት የምንላቸው እንደ ኦቲዝም የመሳሰሉት የሚከሰቱትም በዚህ ሂደት መሆኑን ያነሳሉ፡፡

ሌሎቹ ደግሞ ከውልደት በኋላ የሚከሰቱ ሲሆኑ በአደጋ፣ አልኮል አብዝቶ በመጠጣትና የደም ስር ችግር በመሳሰሉት ክስተቶች የአእምሮ ጤና መቃወስ ሊመጣ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

በአለማችን ካሉ ሰዎች ከስድስት ሰው አንዱን በነርቭ ህመም ሊጠቃ እንደሚችል ደ/ር ያሬድ ይናገራሉ፡፡

ለዚህም ከአለም 7 ነጥብ 8 ቢሊየን ህዝብ ውስጥ አንድ ቢሊየን የሚሆነው በነርቭ ህመም ይጠቃል ተብሎ እንደሚታሰብ በጥናት መረጋገጡን ይገልጻሉ፡፡

የእድሜ መግፋት በነርቭ ስርዓት መዛባት ለሚመጡ ህመሞች የመጠቃት እድልን ከፍ እንደሚያደርግም ዶ/ር ያሬድ አንስተዋል፡፡

የአዕምሮ ጤናን ለመጠበቅ የአለም ጤና ድርጅት የለያቸው የአዕምሮ ጤና ማበልጸጊያ መሳሪያዎች እንዳሉ ጠቅሰው፤ ከነዚህም ውስጥ ማህበራዊ መስተጋብርን መጨመር፣ የአየር ብክለትን መከላከል፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መቆጣጠርና ማከም ዋናዋናዎቹ ናቸው ይላሉ፡፡

በተጨማሪም÷ የሰውነት ክብደትን መቆጣጠር፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መስራትና ካላስፈላጊ ሱሶችና እጾች መቆጠብ፣ ልጆችን በእድሚያቸው ወደ ት/ቤት መላክ፣ ተጓዳኝ የሆኑ በሽተዎችን መከላከል፣ የመስማት አቅምን ማሻሻል የሚሉትን ይጠቅሳሉ፡፡

Exit mobile version