አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ያለው የቁጠባ ገንዘብ መጠን ከ2 ትሪሊየን ብር በላይ ማለፉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢ ሰለሞን ደስታ÷ የሕብረተሰቡ የቁጠባ ባህል ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻልና ለውጥ እየታየበት እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ባንኮችን ጨምሮ በተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት አጠቃላይ የቁጠባ ገንዘብ መጠን 2 ነጥብ 19 ትሪሊየን ብር መድረሱን ገልጸዋል።
የቁጠባ መጠኑ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በ25 በመቶ እድገት ማሳየቱንም ነው የተናገሩት።
ሁሉን አቀፍ የቁጠባ ስርዓት ለመፍጠር በተደረገው ጥረት ሴቶችና አነስተኛና መካከለኛ የሕብረት ስራ ማህበራትን ጨምሮ ሌሎችም የቁጠባ ልምድ እንዲያዳብሩ ተደርጓል ብለዋል።
የዲጂታል ፋይናንስ ስርዓትን በተለያዩ አማራጮች ለሕብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ የቁጠባና የፋይናንስ እንቅስቃሴ እንዲሳለጥ ተደርጓልም ነው ያሉት።
የዲጂታል ስርዓቱ መስፋፋት፣ የአዳዲስ ባንኮች ወደ ስራ መግባት፣ የካፒታል ገበያና የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ የመግባት እድል ተዳምረው ለቁጠባ ማደግ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆኑ መናራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የፋይናንስ ዘርፉን ጨምሮ በሁሉም መስኮች የዲጅታል ቴክኖሎጂን ተግባራዊ በማድረግ በ2025 ዓ.ም ዲጅታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል።