አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ ሀገራት የተሳተፉበት 9ኛው የአፍሪካ ሶርሲንግና ፋሽን ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል፡፡
የንግድ ትርዒቱን ያስጀመሩት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፥ መንግስት በልማታዊ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች የኢትዮጵያን ብልፅግና እውን ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የመንግስት የረጅም ጊዜ ራዕይ ኢትዮጵያን በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ በአፍሪካ ቀዳሚ ሀገር ለማድረግና መካከለኛ ገቢ ያለው ማህበረሰብ መገንባት ነው ብለዋል።
የጨርቃ ጨርቅና ቆዳ ኢንዱስትሪዎች እሴት መጨመር፣ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት፣ የስራ እድል መፍጠር እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማዕከል ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል ።
ኢትዮጵያን የጨርቃ ጨርቅና ፋሽን መናኸሪያ እንድትሆን ከሚያደርጉት ጉዳዮች መካከል የሀገር ውስጥ ገበያ፣ የሰለጠነ የሰው ሃይል እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተደራሽነት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ እና በአጎራባች አፍሪካ ሀገራት ፋሽንን የሚያውቅ ህዝብ ጥራት ያለው የአልባሳትና የጨርቃ ጨርቅ ፍላጎት እያደገ በመምጣቱና የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና እየሰፋ መሆኑ የኢትዮጵያ ምርቶች ፍላጎት የበለጠ እያደገ እንደሚሄድም ነው የገለጹት።
ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ማምረቻ ማዕከል ለማድረግ ጅምር ስራዎችን በመያዝ ትልቅ የኢንዱስትሪላይዜሽን ጉዞ ጀምራለች ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡