የሀገር ውስጥ ዜና

ጃይካ ለኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ

By Amele Demsew

November 03, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጃፓን ዓለም ዓቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሻሻል ለኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ከጃይካ የኢትዮጵያ ተወካይ ኃላፊ ካትሱኪ ሞሪሀራ (ዶ/ር) እና ኦሽማ ከንሱክን ጋር ስለ ካይዘን የልህቀት ማዕከልና የኢትዮጵያ ታምርት ሀገራዊ ንቅናቄ ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይታቸውም÷ ጃፓን ቲዮታ ካምፓኒ ላይ የተተገበረውን ስኬታማ የካይዘን ፍልስፍና ለኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪ የስራ ቅልጥፍናና ውጤታማነት እንዲያግዝ ለምታደርገው መጠነ ሰፊ ትብብርና ድጋፍ አቶ መላኩ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

አዲስ አበባ የተገነባው ሁለገብ የካይዘን የልህቀት ማዕከል ቀጣይነት ያለው የአዕምሮ ግንባታ የአሰራር ስርዓት ማሻሻያ የቅመራ ማዕከል ሆኖ እንዲያገለግል ለማስቻል ራሱን የአሰራር ስርዓት እየተዘጋጀለት መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ቀዳሚ ኢኮኖሚ ምንጭ ለማድረግ የተቀረፀውን ፖሊሲ ለመተግበር የሚያግዙ በርካታ ስትራቴጅዎች መዘጋጀታቸውንም ነው የገለጹት፡፡

ለዚህም የተኪ ምርት፣ የቆዳ ልማት፣ የአቅም ግንባታና የኮሙኒኬሽን ስትራቴጅዎች ጸድቀው ወደ ስራ መገባቱን እንደማሳያነት አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ታምርት ሀገራዊ ንቅናቄን ከግብ ለማድረስ በሚደረገው ጥረት ጃይካ ድጋፍ እንዲያደርግ መጠየቃቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የጃይካ የኢትዮጵያ ቢሮ ዋና ተወካዮች በበኩላቸው÷ ንቅናቄውን ለመደገፍ ከኢትዮጵያ ታምርት ፕሮጀክት ጸ/ቤት ጋር ውይይት መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሻሻል በሚደረገው ጥረትም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን በመደገፍ የድርሻቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ቃል ገብተዋል፡፡