Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የሀገራትን የጋራ ተጠቃሚነት የሚያሳድግ ነው -ምሁራን

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 23 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በሳል የዲፕሎማሲ አካሄድን የተከተለና የማንንም ሀገር ጥቅምና መብት የማይነካ መሆኑን ምሁራን ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ የባህር በር የመጠቀም መብትና የያዘችውን የዲፕሎማሲ አቅጣጫ በማስመልከት አንጋፋው ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና እንዳሉት፥ የባህር በር የመጠቀም መብት የኢትዮጵያውያን የረጅም ጊዜ ጥያቄ ነው፡፡

የቆየውን የሕዝብ ጥያቄ ለመመለስ ደግሞ የሰጥቶ መቀበል መርህንና የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ የዲፕሎማሲ ጥረት ዘመኑን የዋጀና የሀገራትን መብት የማይነካ መሆኑን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ የተከተለችው የዲፕሎማሲ አካሄድ የባህር በር ካላቸው ሀገራት ጋር በድርድርና በስምምነት የመጠቀምና በጋራ የመልማት መርህ መሆኑንም ነው የገለጹት።

በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ የዲፕሎማሲ አካሄድን መከተል ቀጣናዊ ትስስርን መፍጠር የሚያስችል በመሆኑ የኢትዮጵያም አካሄድ በዚሁ መልኩ መቀጠል አንዳለበት ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በተለይም ከአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሀገራት ጋር በትብብርና በሰጥቶ መቀበል መርህ በመሥራት የሕዝቦችን ተጠቃሚነትና የምጣኔ ኃብት እድገት ለማሳለጥ የያዘችውን አቋም አጠናክራ መቀጠል ይኖርባታል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና ዓለም አቀፍ የህግ ምሁሩ ሳዲቅ አደም በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ዓለም አቀፍ ህጎችን መሰረት ያደረገ በመሆኑ በየትኛውም መልኩ ተቀባይነት ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት እንድትሆን ሊደግፍ የሚችሉ ዓለም አቀፍ ህጎች ተደንግገው ያሉ መሆናቸውን አንስተው በእነዚህ ድንጋጌዎች ተጠቅመውም በርካታ ሀገራት የባህር በር ማግኘታቸውን አስረድተዋል፡፡

Exit mobile version