የሀገር ውስጥ ዜና

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እና አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በጋራ ለመስራት ተስማሙ

By Amele Demsew

November 02, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እና አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው እና የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ለሚ ጉታ(ዶ/ር) ተፈራርመዋል።

የመግባቢያ ሰነዱ ተቋማቱ በፕሮጀክቶች ፣በሴሚናሮች፣በቴክኖሎጂ፣በአቅም ግንባታና መሰል ስራዎች ላይ በጋራ መስራት የሚያስችላቸው መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ÷ፋና ከመዝናኛው ዘርፍ ባለፈ ሀገርን የማሳደግና ትውልድን የማነፅ ሀላፊነት አለበት ፤ ነገን የሚያሻግሩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው ።

ከዩኒቨርሲቲው ጋር የተደረገው ስምምነትም የተቋማት ስራዎች ቴክኖሎጂና እውቀት ወደ ህዝብ እንዲደርስ ያለመ ነው ብለዋል፡፡

ተቋሙ በበርካታ አካባቢዎች ተደራሽ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው የሚሰራቸው ስራዎች ለማህበረሰቡ እንዲደርሱና እንዲታወቁ ያደርጋል ብለዋል።

የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ለሚ ጉታ(ዶ/ር)በበኩላቸው ÷ዩኒቨርሲቲው ለማህበረሰብና ሀገር የሚጠቅሙ የምርምር ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው እየሰራቸው የሚገኙ የሳይንስና ቴክኖሎች ስራዎች ለማህበረሰቡ ተደራሽ እንዲሆን ሚዲያው ትልቅ ሚና ያለው ነው ያሉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት “ከፋና ጋር መስራታችን የምርምር ስራዎችን በጋራ ለመጠቀምና ለማስተዋወቅ ይረዳናል “ብለዋል።

በቅድስት አባተ