አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለተወጣጡ ተባባሪ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና መስጠት ጀምሯል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዛሬ በሆሳዕና ከተማ የጀመረው ሥልጠና በአጀንዳ ማሰባሰብና ምክክር ላይ የሚሳተፉ የማሕበረሰብ አባላትን ለመመልመል የሚያግዙትን ተባባሪ አካላት ለለማብቃት ነው ተብሏል፡፡
በሥልጠናው በክልሉ የሚገኙ የሲቪክ ማሕበራት ምክር ቤት ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትና ከሐይማኖት ተቋማት የተወጣጡ አካላት በመሳተፍ ላይ መሆናቸውም ነው የተገለጸው፡፡
ኮሚሽኑ ከዕድሮች ማሕበራት ጥምረት፣ ከመምህራን ማሕበር እንዲሁም ከሁሉም ወረዳና ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች የሚወክሉ ዳኞችን ጨምሮ ከ574 በላይ የማሕበረሰብ ክፍሎችን እንደሚያሰለጥን ተነግሯል፡፡
በማስጀመሪያ መርሐ-ግብሩ ላይ ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ፣ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ(ዶ/ር)ን ጨምሮ ሌሎችም መገኘታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡