የሀገር ውስጥ ዜና

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ እዝ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ከመፍረስ ታድጓል – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

By Amele Demsew

November 02, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ እዝ በሰራው ስራ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ከመፍረስ ታድጓል ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለፀ፡፡

ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ዛሬ በሰጡት መግለጫ÷ እራሱን በፋኖ ስም የሚጠራው ፅንፈኛ ቡድን የአማራ ህዝብ ጥያቄን ሽፋን በማድረግ ኢ-ህገመንግስታዊ አካሄድን በመከተል በሃይልና በነፍጥ፣ በረብሻና በግርግር በመታገዝ በመጀመሪያ አማራ ክልልን ከዛም የፌደራል ስርዓቱን በማፍረስ የራሱን እኩይ ኢኮኖሚያ እና ፖለቲካዊ ፍላጎቶች ለማሳካት አልሞ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ቡድኑ የደቀነውን አደጋ ለመቀልበስም በወቅቱ መደበኛ በሆነ ህግ ማስከበር እንደማይቻል በመረጋገጡ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት እና የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስት ጠቅላይ መምሪያ እዝ በማደራጀት ወደ ተግባር መግባቱንም እንዲሁ አስታውሰዋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ መምሪያ እዙም በልዩ ልዩ አደረጃጀቶች ተደራጅቶ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መግባባት ላይ ተደርሶ ወደ ተግባር ተገብቷል ነው ያሉት፡፡

በየጊዜውም በክልሉ እና በአጎራባች አካባቢዎች የተለያዩ የተወሰዱ ኦፕሬሽኖችን፣ ክልከላዎች፣ የተደረጉ ማሻሻያዎች እንደዚሁም የተገኙ ውጤቶች ለህዝቡ ይፋ እያደረገ መቆየቱንም ነው ያነሱት ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)፡፡

ክልሉን ወደ ነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ የተደረጉ ጥረቶችን እና የአመራር መልሶ ማደራጀት ለህዝቡ ግልፅ እያደረገ መጥቷል ብለዋል፡፡

በትናንትናው ዕለትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ እዝ የእስካሁኑን የትግበራ እንቅስቃሴ መመርመሩን አስታውቀዋል፡፡

በዚኅም በግምገማ ማረጋገጥ የተቻለው ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ከመፍረስ መታደጉን ነው ብለዋል፡፡

ከዚህም በላይ በክልሉ የተጠናከረ አመራር እንዲደራጅ እና የህዝቡን መሰረታዊ ጥቄዎች ለመፍታት ቁመና እንዲላበስ መደረጉ በግምገማው ተገጋግጧል ብለዋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከመታወጁ በፊት ፅንፈኛ ኃይሉ በታጠቁ ሃይሎችና በተዛባ መረጃ የክልሉ ዋና ከተሞች እንቅስቃሴ እንዲሁም ክልሉ ከሌሎች አካባቢዎች ጋር የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች እንዲገታ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተከትሎ የፀጥታ ሃይሎች በወሰዱት ህጋዊ እርምጃ ፅንፈኛው ሃይል ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ ደርሶበታል ብለዋል፡፡

በፕሮፖጋንዳና በብሄርተኝነት የተደናገረው የተለያየ የህብረተሰብ ክፍልም ግንዛቤ ወስዶ ሁኔታውን እየተረዳ በመምጣቱና የመከላከያ ሰራዊት በወሰደው ህጋዊ እርምጃ  ፅንፈኛ ቡድኑ በደረሰበት ምት ወደ ተበታተነ የመንደር ሽፍትነትና ወንበዴነት መቀየሩን ተናግረዋል።

በዚህም የክልሉን የፀጥታ ሃይል መገዳደር ወደ ማይችልበት ደረጃ መውረዱን እዙ በግምገማው አረጋግጧል ብለዋል፡፡