Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የታቀደውን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ለማሳካት ለውሃ አጠቃቀም ትኩረት መስጠት ይገባል- አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን ለማሳካት ለውሃ አጠቃቀም ትኩረት መስጠት እንደሚገባ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡

አቶ ሽመልስ አብዲሳ÷በክልል ደረጃ የበጋ መስኖ ስንዴ በምዕራብና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞኖች አስጀምረዋል።

በዚህ ወቅት አቶ ሽመልስ÷ በክልሉ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ባለፉት ሶስት ዓመታት በስፋት ሲሰራበት መቆየቱን ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት ከ1 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ መልማቱን አስታውሰው÷ ዘንድሮ ደግሞ 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታር መሬት ለማልማት መታቀዱን ገልጸዋል።

ይህንን እቅድ ለማሳካት የክልሉ መንግስት የግብርና ግብዓትን እያቀረበ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

ለበጋ መስኖ ልማት ውሃ ወሳኝ በመሆኑ የግብርና ባለሙያውም ሆነ አርሶ አደሩ ሀብቱን ባግባቡ እንዲጠቀሙ አሳስበዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ በበኩላቸው÷ የዘንድሮውን እቅድ ለማሳካት 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት መታረሱን ተናግረዋል።

ከታረሰው መሬት ውስጥም እስከ ዛሬው ድረስ 525 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር እንደተሸፈነ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በዞኑ ላለፉት ሶስት ዓመታት የበጋ መስኖ ልማት ሲከናወን መቆየቱን የገለጹት ደግሞ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ታዬ ጉዲሳ ናቸው።

ልማቱ ሲጀመር በአንድ ሺህ ሄክታር መሬት ላይ እንደነበረ አውሰተው÷ ዘንድሮ በ105 ሺህ ሄክታር ላይ የበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

Exit mobile version