Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የመዲናዋ ነዋሪዎች ለሰላም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቱሪዝም ዘርፍ ሰላምን የሚፈልግ በመሆኑ የመዲናዋ ነዋሪዎች ለሰላም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የሥራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱሥትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር ዓባይ ጥሪ አቀረቡ፡፡

በዓለም ለ44ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ36ኛ ጊዜ የተከበረው የቱሪዝም ሣምንት ዐውደ-ርዕይና ባዛር የመክፈቻ መርሐ-ግብር በመስቀል አደባባይ ተካሂዷል፡፡

አቶ ጃንጥራር በመርሐ-ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ቱሪዝም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በርካታ የጎብኚ መዳረሻ ላላቸው ሀገራት የዕድገት መሰላል ሆኖ እያገለገለ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ዘርፉ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ከተማ እንዲስፋፋ ያሉንን ጸጋዎች ማወቅና ማሳወቅ ትልቁ ሥራ ነው ማለታቸውን የሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱሥትሪ ልማት ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡

የቱሪዝምን ሣምንትን ስናከብርም በሀገራችን ብሎም በመዲናችን ቀጣይነት ያለው ዕድገት ለማረጋገጥ በሚደረገው ሂደት ቱሪዝም አካታችና ሁሉንም የሚያቅፍ ዘርፍ መሆኑን በመገንዘብ መሆን አለበት ነው ያሉት፡፡

የከተማችን ነዋሪዎች ይህን ታላቅ እድልና ጠቀሜታ ያለውን ዘርፍ በሚገባ ተገንዝባችሁ ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እራሳችሁንና ሀገራችሁን ለመጥቀም በተነሳሽነት እንድትሠሩ ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ቱሪዝም ብቻውን የሚለማ ባለመሆኑ ቅንጅታዊ አሠራርን በመዘርጋት የሀገራችንን የገቢ ምንጭ ማሣደግ እንደሚገባና የቱሪዝም ዘርፍ ከምንም በላይ ሰላምን የሚፈልግ በመሆኑ ለሰላም የምንታትር ሕዝቦች መሆን ይገባናል ብለዋል በንግግራቸው፡፡

የከተማችን ነዋሪዎች ሰላም የሁሉም መሰረት መሆኑን በመገንዘብ የቱሪዝም ዘርፉ እንዲያብብ የበኩላችሁን እንድታበረክቱ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version