የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ ከቆዳና ሌጦ ምርት ማግኘት የሚገባትን ያህል ገቢ እያገኘች አለመሆኑ ተገለጸ

By Amele Demsew

October 31, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር አቀፍ ደረጃ በዓመት ከሚመረተው 41 ሚሊየን በላይ የቆዳና ሌጦ ምርት ውስጥ ከ22 ሚሊየን ያልበለጠው ብቻ ለአገልግሎት እንደሚውል የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በቆዳ ልማት ስትራቴጂ ሰነድ ላይ ከመንግስት የሥራ ሃላፊዎች ፣ ባለድርሻ አካላትና በዘርፉ ከተሰማሩ የአምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶች ጋር ውይይት እያደረገ ነው፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ÷ የቆዳ ዘርፍ ላለፉት አመታት በርካታ ችግሮች የሚነሱበትና መፍትሄ እንዲሰጥ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲቀርብበት የቆየ ዘርፍ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከ165 ሚሊየን በላይ የቀንድ ከብት ሃብት ያላት ቢሆንም በሚፈለገው ልክ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ያህል ገቢ እያገኘች አይደለም ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።

የቆዳ ፋብሪካዎቹ ከጥሬ እቃ አቅርቦት በተጨማሪ በማሰባሰብ እና ከአጓጓዝ ሂደት ጋር በተያያዘ በሚያጋጥሟቸው ችግሮች ምክንያት ባክኖ የሚቀረው ምርት በርካታ መሆኑንም ነው የገለጹት።