አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሞስኮ የኤሌክትሮኒክስ መደብር ለመስራት የተቀጠረው ግለሰብ ሥራ በጀመረበት ዕለት መደብሩን ‘በስርቆት አጽድቶ’ በቁጥጥር ስር መዋሉ አነጋጋሪ ሆኗል።
የ44 አመቱ ሩሲያዊ ግለሰብ በወሩ መጀመሪያ በሞስኮ በሚገኝ አንድ የኤሌክትሮኒክስ መደብር ውስጥ በሽያጭ ስራ አስኪያጅነት ተቀጥሮ ሥራውን ይጀምራል።
ስሙ ያልተጠቀሰው ይህ ግለሰብ ሥራ በጀመረበት የመጀመሪያ ቀን ታዲያ የመደብሩን ዘመናዊ 53 አይ ፎን ስልኮች ከተቀጠረበት መደብር በመዝረፍ መነጋገሪያ ሆኗል።
ግለሰቡ ሥራ በጀመረበት ዕለት 53 ዘመናዊ አይ ፎን ስልኮችን እና 53 ሺህ ሩብል (የሩሲያ መገበያያ ገንዘብ) ከመደብሩ በመዝረፍ መሰወሩን የሩሲያ የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር ባጋራው አጭር ተንቀሳቃሽ ምስል አስታውቋል።
የፖሊስ ምንጮች እንደገለፁት የ44 ዓመቱ ሰው በኤሌክትሮኒክስ መደብር ውስጥ የሽያጭ ስራ አስኪያጅ ሆኖ የተቀጠረው በሀሰተኛ ማስረጃ ነበር፡፡
የመደብሩ ሁሉም ቁልፎች በእጁ ስለነበሩም ቀደም ብሎ በመግባት 53 አዳዲስ አይፎኖችን እና በካዝና ያለውን ገንዘብ በሙሉ ወስዶ ከተማዋን ለቆ ወደ መኖሪያው ሴባስቶፖል ከተማ ያቀናው ግለሰብ በመረጃው መሰረት በፍጥነት ተለይቶ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሏል።
ፖሊስ ግለሰቡ ቤት ውስጥ ባደረገው ፍተሻም የተወሰኑ እቃዎችን እንጅ ሁሉንም ስልኮች ማግኘት አልቻለም፤ ምክንያቱም ግለሰቡ ወደ ቤቱ እስከሚመለስ ድረስ መንገድ ላይ የተወሰኑትን ሸጧቸው ነበርና።
አሁን ላይ ግለሰቡ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ በፈፀመው የስርቆት ወንጀል ክስ ተከፍቶበት ዘብጥያ መውረዱ ተገልጿል።
ዝርፊያ የተፈጸመበት የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች መሸጫ መደብር ወደ 3 ሚሊየን ሩብልስ የሚደርስ ኪሳራ እንደከሰረ አስታውቋል።
የአስተዳደር ክፍሉም ከዚህ በኋላ የሥራ አመልካቾችን የምስክር ወረቀቶችንና ትምህርት ማስረጃዎችን በጥንቃቄ የማረጋገጥ ሥራ እንደሚሰራ ማመላከቱን ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል፡፡
የ44 አመቱ ጎልማሳም የቅጥር ፊርማው ሳይደርቅ ስርቆት የፈጸመ የመጀመሪያው ሰው ሆኖ ተመዝግቧል።