የኢትዮ-ጅቡቲ ትራንስፖርት ፍሰት ደህንነቱ ተጠብቆ እንዲከናወን በትኩረት እየተሰራ ነው

By Melaku Gedif

October 30, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮ-ጅቡቲ ትራንስፖርት ፍሰት ሠላማዊና ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ እንዲከናወን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የአፋር ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ አስታውቋል፡፡

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ሁሴን ቦልኮ እንደገለጹት÷ የሀገሪቱን ቁልፍ የገቢና ወጪ ንግድ የትራንስፖርት እንቅስቃሴን የተሳለጠ ለማድረግ የተለያዩ የእርምት እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው።

በዚህ መሰረትም ከሕግ አግባብ ውጭ በተለያዩ አካባቢዎች አሽከርካሪዎችን ሲያስቸግሩ የነበሩ የመንገድ ተቆጣጣሪዎችን ከሥራ ማገድ ጨምሮ በሕግ እንዲጠየቁ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

ቢሮው የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን አስተባብሮ የተበላሹ መንገዶችን ጊዜያዊ መፍትሄ ለመስጠት የጥገና ሥራ ማከናወኑንም ነው የገለጹት፡፡

በቀጣይ አሽከርካሪዎችና ባለንብረቶች ነጻነታቸውና ደህንነታቸው በተረጋገጠ አግባብ ሥራቸውን እንዲከውኑ ለማስቻል በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በተለይም በአደጋ ግዜ ከሚፈጸሙ የካሳ ክፍያዎች ጋር በተያያዘ ከአሽከርካሪዎች የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመቅረፍ ከሀገር ሽማግሌዎችና የፍትሕ ተቋማት ጋር እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የክልሉ ትራፊክ ፖሊስ በበኩሉ÷ የኢትዮ-ጅቡቲ አሽከርካሪዎችን ደህንነት ለማረጋገጥ ከቁጥጥር ጀምሮ በርካታ ሥራዎች እየተከናወነ ነው ማለታቸውን የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል፡፡