የሀገር ውስጥ ዜና

ለ2016/17 የምርት ዘመን ግብዓት የሚሆን የአፈር ማዳበሪያ ማጓጓዝ ተጀመረ

By Shambel Mihret

October 30, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2016/17 የምርት ዘመን ግብዓት የሚሆን የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ሥራ መጀመሩን የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ገለጸ፡፡

የምርት ዘመኑን የአፈር ማዳበሪያ የጫነች የመጀመሪያዋ መርከብ ትናንት ምሽት ጅቡቲ መድረሷ ተገልጿል፡፡

ኦሞርፊ ማጁሮ የተባለቸው መርከብ ለ2016/17 የምርት ዘመን ወደ ሀገር ውስጥ ከሚገባው የአፈር ማዳበሪያ የመጀመሪያውን 51 ሺህ 420 ሜትሪክ ቶን ዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ ከግብጽ አዳቢያ ወደብ ጭና ትናንት ምሽት ጅቡቲ ኤስ.ዲ.ቲቪ ወደብ ገብታለች ተብሏል፡፡

ወደብ የደረሰውን የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ የመጫን እና የማጓጓዝ ስራም እንደተጀመረ ተጠቅሷል፡፡

ድርጅቱ የአፈር ማዳበሪያን ከመጫኛ የባሕር ወደብ እስከ አርሶ አደሩ ድረስ የማድረስ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑንም የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት መረጃ ያመላክታል፡፡

ለ2016/17 ምርት ዘመን 23 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በግዢ ለማቅረብ መታቀዱን ከዚህ ቀደም የገለጸው የግብርና ሚኒስቴር፤ የኤንፒኤስ ማዳበሪያን ጨምሮ 13 ሚሊየን ኩንታል መገዛቱን መግለጹ ይታወሳል።