አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 17 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሕገ-ወጥ የወርቅ አምራቾችና አዘዋዋሪዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።
አቶ አሻድሊ ሀሰን በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የወርቅ አምራች ማኅበራትን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
ርዕሰ-መስተዳድሩ ክልሉ ከሚታወቅባቸው የማዕድን ሀብቶች ቀዳሚው ወርቅ መሆኑን ጠቁመው፥ መንግስት በዘርፉ የሚሳተፉ ሕገ-ወጥ አምራችና አዘዋዋሪዎችን ስርዓት ለማስያዝ ግብረ-ኃይል አቋቁሞ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባውን የወርቅ መጠን ለማሳደግ ባለፉት ጊዜያት በተሠሩ የሕግ ማስከበር ሥራዎች አበረታች ውጤት ተመዝግቧል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።
በጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ብቻ ከባህላዊ ወርቅ አምራቾችና ከአነስተኛ ማኅበራት ከ100 ኪሎ ግራም በላይ (1 ነጥብ 4 ኩንታል) የወርቅ ምርት ወደ ብሔራዊ ባንክ መግባቱንም አስታውሰዋል።
መንግስት በሕገ-ወጥ የወርቅ አምራቾችና አዘዋዋሪዎች ላይ የጀመረውን እርምጃ ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።