Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያ ያቀረበችው የባሕር በር ጥያቄ አግባብነት አለው – የፖለቲካ ፖርቲ አመራሮች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ አግባብነት ያለውና ታሪካዊ መብት ጭምር መሆኑን የኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ፡፡

የተነሳው የባሕር በር ተጠቃሚነት ጉዳይ ያለ ልዩነት የሁሉም አጀንዳ መሆን እንደሚገባውም አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያ የባሕር በር ተጠቃሚ ልሁን ብላ ያቀረበችው ጥያቄ በየትኛውም መመዘኛ ቢለካ ትክክል መሆኑን የኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀ- መንበር ግርማ በቀለ ገልጸዋል፡፡

ጉዳዩ ከዚህ በፊትም ሲነሳ እንደነበረ አስታውሰው÷ አሁንም ከኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ አለመውረዱን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ምክትል ሰብሳቢ ራሄል ባፌ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ የባሕር በር አልባ መሆን ታሪካዊ ስህተት እንደነበር በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ሀገሪቱ የባሕር በር ባለቤት እንደነበረች ያስታወሱት አመራሮቹ÷ አሁንም ጉዳዩን ማንሳቷ አግባብነት ያለው መሆኑን አንስተዋል፡፡

የጥያቄው አግባብነት አጠያያቂ ባይሆንም ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ የሚደረግበት መንገድ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገውም ነው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያስረዱት፡፡

አካባቢያዊ እና ቀጣናዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነታችንን ታሳቢ ያደረገ አቅጣጫ እንዲቀመጥ ጠይቀው÷ በጉዳዩ ላይ ከሕዝብ ጋር ምክክር ማድረግ እንደሚገባም መክረዋል፡፡

በሰሎሞን ይታየው

Exit mobile version