አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ለጡት ካንሰር በሽታ ልየታ እና ምርመራ የሚረዳ ሞዴል መስራቱ ተሰምቷል፡፡
ለብዙዎች ሞት መንስዔ የሆነው የጡት ካንሰር በሽታ ቀድሞ ከተደረሰበት የመዳን እድሉ ከፍተኛ እንደሆነ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ማንኛውም ታካሚ ወደጤና ተቋም በመሄድ ማሞግራፊ ያለበት ቦታ የጡት ካንሰር ምርመራ ሊያደርግ ይችላል፡፡
ከዚህ ቀደም በማሞግራፊ ምርመራ ካደረጉ በኋላ የሚገኘው ምስልን ለማንበብ ጊዜ ይወስዳል፡፡
ሆኖም ይህ ሞዴል ምስሉ ከተገኘ በኋላ ካንሰሩ ያለበትን ቦታ ለይቶ እና ደረጃውንም ለይቶ ያለውን ውጤት እንደሚያወጣም ከኢንሰቲትዩቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ይህም ከጊዜ አንጻር ያለው ጠቀሜታ ከፍ ያለ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ፥ ድካምን በማስቀረትም አስተዋጽዖ እንዳለው ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ ካለው የዘርፉ ባለሙያዎች እጥረት ጋር ተያይዞ እንዲሁም የታካሚው ቁጥር መጨመር በሚታይበት ወቅት የቴክኖሎጂ ሞዴሉ በሽታው ያለበትን ሁኔታ ለማወቅ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለውም ነው የተነገረው፡፡