ዓለምአቀፋዊ ዜና

ለመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት ፖለቲካዊ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል – ፕሬዚዳንት ማክሮን

By Alemayehu Geremew

October 25, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካረረ ላለው ግጭት ፖለቲካዊ መፍትሄ ሊበጅለት እንደሚገባ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑዔል ማክሮን አሳሰቡ፡፡

ፕሬዚዳንቱ ከግብጹ አቻቸው አብዱልፈታህ አል ሲሲ ጋር በመሆን በካይሮ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫውም ሽብርተኝነትን መዋጋት፣ የማኅበረሰብን ደኅንነት መጠበቅ እና ለችግሩ ፖለቲካዊ መፍትሄ ማበጀት ዋና ዋና ጉዳዮች ናቸው ብለዋል።

ዓለም አቀፉ ሕግ ለሁሉም እኩል እንደሚሰራና ፈረንሳይም ሰብዓዊ ዕሴቶች ለሁሉም እኩል መከበር እንዳለበት እምነቷ መሆኑን ተናግረዋል።

ለሁሉም ተጠቂዎች እንራራለን፤ አንዱን ከአንዱ የምንለይበት ሁኔታ የለም በማለት ገልጸው፤ መካከለኛው ምሥራቅ ዘላቂ ሠላም ያሻዋልም ሲሉ ነው ያሰመሩበት፡፡

የሕክምና አቅርቦት የጫነ አውሮፕላን ግብፅ እንደሚደርስም ነው የተናገሩት፡፡

በቅርቡ በጋዛ ሆስፒታሎች ያለውን የሕክምና አቅርቦት ችግር ለማቃለል ፈረንሳይ መድሐኒት በመርከብ እንደምታደርስ አረጋግጠዋል፡፡

ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲም ጦርነቱ አደገኛ እንደሆነና ለበርካቶች ሕይወት መጥፋት መንስዔ እንደሚሆንም ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

በእስራዔል- ሀማስ ጦርነት እስካሁን ቢያንስ 6 ሺህ 546 ፍልሥጤማውያን እና 1 ሺህ 400 እስራዔላውያን በጠቅላላው ከ7 ሺህ 900 በላይ ንጹሐን ሰዎች መገዳላቸውን አናዱሉ ዘግቧል።