አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኳታር በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ተሰማርቶ የሚገኘው ግዙፉ የሱሀይል ግሩፕ ኩባንያ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለው ገለጸ።
በኳታር፣ በኢራንና በየመን የኢትዮጵያ አምባሳደር ፈይሰል አልይ ከኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ዚያድ ኢሳ አቦክሎብ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ ወቅት የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ እንዳሉት÷ ኩባንያው በኢትዮጵያ የመኪና ባትሪን መልሶ በማምረት ጥቅም ላይ በማዋል ዘርፍ ለመሰማራት ቅድመ ዝግጅቱን ጨርሶ ግንባታ ጀምሯል።
ፕሮጀክቱን ለማስፋትም ፍላጎት እንዳለው አመልክተዋል።
አምባሳደር ፈይሰል አልይ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ቅድሚያ በሰጠቻቸው የኢንዱስትሪ ዘርፎች ያለውን የኢንቨስትመንት ዕድሎች በተመለከተ ገለፃ ማድረጋቸውን ከዶሃ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ከውይይቱ ቀደም ብሎ በአምባሳደር ፈይሰል አልይ የሚመራው የኤምባሲው ልዑካን ቡድን ኩባንያው ካሉት 13 ኩባንያዎች መካከል አራቱን የማምረቻ ፋብሪካዎች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።