አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊትን በሙያቸው ያገዙ ግለሰቦች የክብር አባልነትና እና ዕውቅና ተሠጠ።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ሳንጠጋቸው የተጠጉን ሳንደግፋቸው የደገፋን የሰፈር ንፋስ ሳያወዛውዛቸው በፅኑ ከሠራዊቱ ጎን መቆሙን ማረጋገጡን ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት 116ኛውን የሠራዊቱን በዓል በማስመልከት በተለያየ መልኩ ለሠራዊቱ በሙያቸው ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ ግለሰቦችን የክብር አባል በማድረግ እውቅናም ሰጥቷል።
በዚህ ዓይነቱ ባልተለመደና እንደሀገር የመጀመሪያ በሆነው ዕውቅና ከሀያ በላይ ለሆኑ የማህበረሰብ አንቂዎች፣ ጋዜጠኞችና የበጎ አድራጎት ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችና ባለሙያዎች ናቸው ይህ የሰራዊት የክብር አባልነት የተሰጣቸው።
የሰራዊቱ የክብር አባል ማድረጊያ በአዋጅ ተደንግጎ የተቀመጠ መሆኑንና በመመሪያው መሰረት ለመጀመሪያ ጊዜ የተከናወነ መሆኑም ተገልጿል።
እውቅና የተሰጣቸው ግለሰቦች በሰራዊቱ ላይ የሚሰነዘሩ የማኅበራዊ ሚዲያ ጥቃቶችን ሲከላከሉና ሲጋፈጡ እንዲሁም ሲመክቱ የነበሩ መሆናቸው ተመላክቷል።
የጠላት ሴራ እንዳይሳካ ሌት ተቀን ከሰራዊቱ ጋር ሲሰሩ የነበሩ መሆናቸውም ተጠቅሷል።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ÷ ይህንን እውቅና ያገኙ አካላት በሥራቸው የሰራዊቱን መልካም ሥነ-ምግባር እንዲሁም ዝና በማስገንዘብ ስሙን ለማጠልሸት ከሚሯሯጡ የጠላት አካላት ታድገዋል ብለዋል።
በቀጣይም በተመሳሳይ ተግባራት ላይ ለሚሳተፉ አካላት ይህ እውቅና እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
የመከላከያ ሰራዊት ማለት አገር ማለት ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የአገር መከላከያ ሰራዊትን ማክበር ኢትዮጵያን ማክበር ነው ብለዋል።
በበረከት ተካልኝ