ዓለምአቀፋዊ ዜና

ዓለም ወደታዳሽ ኃይል የምታደርገው ጉዞ የሚገታ እንዳልሆነ ተመላከተ

By Meseret Awoke

October 25, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ ዓለም ወደታዳሽ ኃይል የምታደርገው ጉዞ የሚቆም እንዳልሆነ ባወጣው ሪፖርት ገለጸ፡፡

ኤጀንሲው ዓለም የታዳሽ ኃይል ላይ እያስመዘገበች ያለውን ቀጣይነት ገልጾ፥ ሆኖም ግን የቅሪተ አካላት ነዳጅ አጠቃቀም አሁንም በሚፈለገው ፍጥነት እየቀነሰ እንዳልሆም ነው የገለጸው፡፡

በዚህም ከ1 ነጥብ 5 ሴንቲ ግሬድ ገደብ በላይ የሙቀት መጠን መጨመርን ለመከላከል አሁንም የካርበን ልቀት በጣም ከፍተኛ እንደሆነ ጠቅሷል፡፡

እናም ሪፖርቱ በከርሰ ምድር ነዳጅ ላይ የሚደረገው ኢንቨስትመንት በግማሽ መቀነስ እንዳለበትም ነው የገለጸው፡፡

በነዳጅ ላይ ያለው ጥገኝነት ከ70 ዓመታት በኋላ የዓለም አማካይ የሙቀት መጠንን ወደ 2 ነጥብ 4 ሴንቲ ግሬድ ሊያሳድገው ይችላል ተብሏል።

በፈረንጆቹ 2015 የዓለም መሪዎች የሙቀት መጨመርን ቢቻል ከ1 ነጥብ 5 ሴንቲ ግሬድ በታች ካልሆነም በ2 ሴንቲ ግሬድ ለመገደብ የተቻለውን ሁሉ ለማድረግ ቃል መግባታቸው ይታወሳል፡፡

ይሕም የዓየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣውን ተጽዕኖ ለማስቀረት እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡

በቀጣዩ ወር የተባበሩት መንግስታት የኮፕ-28 ጉባዔ የዓለም መሪዎች በዱባይ በመሰባሰብ የዓለም የአየር ንብረት ለውጥን አስመልክተው ይሰባሰባሉ፡፡

የኤጀንሲው ውጥረቱ እየጨመረ መምጣቱ በዓለም ኢነርጂ ገበያ ላይ ምን ዓይነት ተጽዕኖ እንደሚያሳድር እስካሁን ግልፅ እንዳልሆነ ተናግሯል።

በዚህም የዓለም የጋዝ ዋጋ ተለዋዋጭ እንደሆነም ነው ኤጀንሲው በሪፖርቱ ያነሳው።

ሆኖም ግን ኤጀንሲው የፀሐይ እና የንፋስ ሃይል መስፋፋት ለኃይል ተለዋዋጭነት የረዥም ጊዜ መፍትሄ እንደሚሰጥ እምነት አለን ሲልም ነው የገለጸው።