የሀገር ውስጥ ዜና

የአማራና ኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተፈናቃዮችን መልሶ በማቋቋም ዙሪያ መከሩ

By Amele Demsew

October 24, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ቡድን ባሕር ዳር በመገኘት ከአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር መክረዋል።

ባለፉት ዓመታት ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎችና በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን በምክክሩ ወቅት ተገልጿል።

በጥፋት ኃይሎች ጥቃት ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉና ሐብት ንብረታቸው የወደመባቸውን ወገኖች በመለየት በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር አብረው ከኖሩት የኦሮሞ ሕዝብ ጋር አብሮነታቸውን ለማስቀጠል ቅንጅታዊ ጥረት እንደሚያስፈልግም ተወያይተዋል።

የሁለቱን ክልል ሕዝቦች አንድነትና አብሮነት የሚጻረሩ ኃይሎችን በመታገል የዜጎችን ደኅንነትና ሐብት ንብረት የማፍራት ነጻነትን ማረጋገጥ እንደሚገባም መግባባት ላይ መድረሳቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

ተፈናቃዮች እያሳለፉት ያለውን ችግር ያገናዘበ ፈጣን ስምሪት በመውሰድ ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲመለሱ የማድረግ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲደረግም አቅጣጫ አስቀምጠዋል።