ዓለምአቀፋዊ ዜና

እስራዔልና ፍልሥጤምን ለማሸማገል ቻይና የሚቻላትን ሁሉ እንደምታደርግ ገለጸች

By Alemayehu Geremew

October 24, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እስራዔል እና ፍልሥጤምን ለማሸማገል ቻይና የሚቻላትን ሁሉ እንደምታደርግ አስታወቀች፡፡

የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ እንዳሉት ÷ ሽምግልናው ሀገራቱን ወደ ሠላም የሚያደርስ እስከሆነ ድረስ ቻይና ማንኛውንም የመፍትሄ እርምጃ አጥብቃ ትደግፋለች፡፡

ዋንግ እስራዔል በመካከለኛው ምሥራቅ ቀጣና የሚገኙ ቻይናውያንን እና ተቋማትን ደኅንነት እንድታረጋግጥ ጥሪ ማስተላለፋቸውን ታይምስ ላይቭ ዘግቧል፡፡

አያይዘውም ሀገራት እራሳቸውን የመከላከል እና ደኅንነታቸውን የማረጋገጥ መብት እንዳላቸው ጠቅሰው ዓለምአቀፋዊ ሰብዓዊ ሕጎች እና የንጹሐን ደኅንነት ግን መጠበቃቸውን ማረጋገጥ ያሥፈልጋል ብለዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በእስራዔል-ፍልሥጤም ግጭት ንጹሐን ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ያወገዙ ሲሆን የእስራዔልን እርምጃ “ራሥን ከመከላከል ያለፈ ነው” ብለውታል፡፡

ቻይና ውጤታማ የሆነ ዓለምአቀፍ የሠላም ጉባዔ በቅርቡ እንዲካሄድ መጠየቋንም ዋንግ ዪተናግረዋል።

ቻይና እና ሩሲያ በሀገራቱ ግጭት የንጹሐን ሕይወት መቀጠፍ ያሳስበናል የሚል አቋም አላቸው፡፡

አሜሪካ በበኩሏ እስራዔል ራሷን የመከላከል መብት አላት የሚል ሐሳቧን አጠናክራ የሃማስን ጥቃት ታወግዛለች።

ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ተንታኞች ደግሞ በሃማስ የሮኬት ጥቃት አንድ ብሎ የተጀመረውና በጋዛ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ አስከትሏል በተባለው ግጭት ሃገራት ጎራ ለይተው በመግባት ቀውሱን እንዳያባብሱት በሚል ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።