የሀገር ውስጥ ዜና

የአውሮፓ ህብረት የናይል ወንዝና የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ላላቸው ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ እውቅና እንደሚሰጥ ገለፀ

By Tibebu Kebede

May 19, 2020

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአውሮፓ ህብረት የናይል ወንዝ እና የታላቁ የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ላላቸው ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ እውቅና እንደሚሰጥ ገለፀ።

የአውሮፓ ካውንስል እና የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዚዳንቶች በጋራ ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በፃፉት ደብዳቤ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ሲደረጉ የነበሩ የሶስትዮሽ ድርድሮችን ህብረቱ ሲከታተል መቆየቱን እና ከሀገራቱ ጋርም ግኑኝነት እንደነበረው ገልፀዋል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባገኘው መረጃ መሰረት ፕሬዚዳንቶቹ በደብዳቤው ድርድሮቹን የህብረቱ አባል ሀገራትም ሲከታተሉት መቆየታቸውን ነው ያመለከቱት።

አሁንም ያልተፈቱ ጉዳዮች መኖራቸው እንደተገነዘቡ በመጠቆሙም በዚህ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ሁሉም ወገን ጉዳዩን በተመለከተ ዋልታ ረገጥ አቋምን አስወግዶ ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ የሚያደረግ ስምምነት ለማግኘት ወደመነጋገሩ እንዲመጡ የአውሮፓ ህብረት እንደሚያበረታታ አስታውቀዋል።

የአውሮፓ ህብረት የናይል ውሃ እና የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ እንዳላቸው ሙሉ በሙሉ እውቅና እንደሚሰጥም አረጋግጠዋል።

ህብረቱ ይህን ጉዳዩን ለመፍታት በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አስተዳደር ላይ የካበተ ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎቹን ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑንም ነው ያመለከቱት።

የትኛወም ወገን ወደ ድርድር እንዲመጣ ሁሉንም እድሎች ህብረቱ መጠቀሙን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በአውሮፓ ህብረት እና በኢትዮጵያ ብሎም በህብረቱ እና አፍሪካ መካከል ላለው ትብብር ከዚያም አለፍ ብሎ በሌሎች ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ያለውን ትብብር ለማሳደግ ይቻል ዘንድ ሁኔታዎች ሲፈቅዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በብራሰልስ ጉብኝት እንዲያደርጉም ግብዣ አቅርበዋል።

በቅርቡ በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ መካከል በአሜሪካ ሲካሄድ የነበረው ድርድር ፍሬ ማጣቱን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ልዩ መልዕክተኛን ወደ ብራሰልስ በመላክ የኢትዮጵያን አቋም ለህብረቱ ግልፅ ማድረጋቸው ይታወሳል።