አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የ“ቤልት ኤንድ ሮድ ፕሮጀክት” አካል በሆነው የኢትዮ- ጂቡቲ የባቡር አገልግሎት የወጪ ንግዷን እያሳለጠች መሆኗ ተመላክቷል፡፡
የኢትዮጵያን የተመረጠ ቡና እና ሌጦ ከአዲስ አበባ ወደ ጂቡቲ ወደብ በማድረስ ረገድ የኢትዮ- ጂቡቲ የባቡር አገልግሎት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ተገልጿል፡፡
ቻይና ይፋ ያደረገችው የ”ቤልት ኤንድ ሮድ ፕሮጀክት” ከመተግበሩ በፊት ኢትዮጵያ የወጪንግዷን ከአዲስ አበባ ጂቡቲ ለማድረስ ቢያንስ ሦስት ቀናት ይፈጅባት እንደነበር ያስታወሰው የሲ ጂ ቲ ኤን ዘገባ÷ ፕሮጀክቱ መተግበር ከጀመረ ወዲህ ግን ከ20 ሠዓታት ባነሰ ጊዜ እንደምታደርስ ጠቁሟል፡፡
የባቡር አገልግሎቱ እውን መሆን የሀገሪቷን የጭነት ወጪ ቢያንስ በአንድ ሦስተኛ እንደቀነሰም አመላክቷል፡፡
የ”ቤልት ኤንድ ሮድ ፕሮጀክት” አካል የሆነው ይሄው የባቡር መሥመር የመንገደኞች እና የጭነት አግልግሎት መሥጠት እንዲያስችል ሆኖ መዘርጋቱንም ነው ያስታወሰው፡፡
በባቡር እስከ ጂቡቲ ወደብ የሚደርሰው በኢትዮጵያ የተመረተ (ሜድ ኢን ኢትዮጵያ) የሚል ወጪ ንግድ÷ በባሕር ወደ እሲያ እና አውሮፓ መላክ የሚያስችል የባቡር-ባሕር ጥምር የትራንስፖርት አገልግሎት ዕውን ማድረግ እንደሚያስችልም ዘገባው ጠቁሟል፡፡
ለቀጣናዊ የምጣኔ ሐብት ልማት ያለውን ከፍተኛ አበርክቶ የተገነዘበው የዓለም ባንክ በ2023 የአዲስ-ጂቡቲ ኮሪደርን የበለጠ ለማሳደግ የሚያስችል ዕርዳታ ማፅደቁ ይታወቃል፡፡
የኢትዮ- ጂቡቲ የባቡር አገልግሎት መጀመር ከኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ግንባታ ዕውን መሆን እና ሥራ መጀመር ጋር ተጣምሮ በኢትዮጵያ ብልጽግናን ዕውን ለማድረግ የተጀመረውን ግሥጋሴ አግዟል ብሏል ዘገባው፡፡