አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ ማዕከላት ሲሰጥ የነበረው ሁለተኛው ዙር የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ስልጠና ተጠናቋል፡፡
ሰልጣኞች ከስልጠናው ያገኙትን ግብዓት ተግባራዊ በማድረግ የሕዝቡን እርካታ በሚያረጋግጥ ሁኔታ በሰላም፣ በልማትና በመልካም አስተዳደር ሥራዎች ላይ በይበልጥ ውጤት ለማምጣት እንዲተጉ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ አሳስበዋል፡፡
እንዲሁም “ሁለንተናዊ ብልጽግና የማረጋገጥ ጉዟችንን እንድታፋጥኑ አደራ እላለሁ” ብለዋል በመልዕክታቸው፡፡
በ10 ከተሞች ለ12 ሺህ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ለ12 ቀናት ሲሰጥ የቆየው ስልጠና በስኬት መጠናቀቁን ገልጸው÷ ስልጠናው በታቀደው መሰረት በውጤታማነት እንዲካሄድ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አካላትን አመስግነዋል፡፡
“ስልጠናው የአመራሩን አቅም በከፍተኛ ደረጃ የገነባ፣ ፓርቲያችንንና መንግስታችንን የሚያጠናክር እንዲሁም የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድግ ነው” ሲሉ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸዋል፡፡