አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም መርማሪ ቦርድ በአማራ ክልል ተፈጠሮ በነበረው የጸጥታ መደፍረስ ሳቢያ በወንጀል ተጠርጥረው በአዋሽ አርባ የማቆያ ማዕከል የሚገኙ ተጠርጣሪዎችን የሰብዓዊ አያያዝ ሁኔታ ተመልከተ፡፡
ከምልከታው ጎን ለጎንም የቦርዱ አባላት ከተጠርጣሪዎቹ ጋር ውይይት አድርገዋል።
በውይይታቸው ወቅትም÷ በአማራ ክልል በተከሰተው የጸጥታ መደፍረስ ተሳትፎ የነበራቸውን ተጠርጣሪዎች ለይቶ ለፍርድ ከማቅረብ አኳያ የምርመራ ሂደቱን በማፋጠን ለፍርድ ማቅረብ እንደሚገባ ተጠርጣሪዎቹ ማንሳታቸውን የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ነጃት ግርማ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ÷ ምግብ፣ ውኃ፣ ንጹሕ መኝታ እንዲሁም የቴሌቪዥን እና የስልክ አገልገሎቶችን እያገኙ መሆናቸውንም አይተናል ብለዋል፡፡
ከሰብዓዊ መብት ጋር በተያያዘ ተጠርጣሪዎቹ የሚደርስባቸው በደል አለመኖሩን የቦርዱ አባል አብረሃም በርታ (ዶ/ር) ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው÷ በወንጀል ተሳታፊ የሆኑን አጣርቶ ለፍርድ ከማቅረብ እና ተሳትፎ የሌላቸውን ወደቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ ከማድረግ አኳያ የምርመራ ሂደቱ እንዲፋጠን ጠይቀዋል፡፡