የሀገር ውስጥ ዜና

የቻይና – አፍሪካ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና መድረክ እየተካሄደ ነው

By Alemayehu Geremew

October 22, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይና – አፍሪካ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና የልምድ ልውውጥ መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

መድረኩ የቻይና – አፍሪካን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር የተደረገው ስምምነት ወደ ተግባር የተገባበት ማሳያ መሆኑን የሥራና ክኅሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ቻይና በሰው ኃይል ልማት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በመምህራን ስልጠና ዘርፎች የምታደርገውን ድጋፍ ማጠናከሯንም ነው የገለጹት፡፡

የቻይና – አፍሪካ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ጥምረት ዋና ዳይሬክተር ማርክ ጎንግ ዙዉ በበኩላቸው÷ ለቻይና ዕድገት የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ትልቅ ሚና አበርክቷል ማለታቸውን የሥራ ክኅሎት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገትና ለዜጎች የሥራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም አስገንዝበዋል፡፡

ቻይና በኢትዮጵያ የቴክኒክና ሙያ መስክ ቴክኖሎጂ ማሸጋገርን ጨምሮ የተለያዩ ስልጠናዎችን እየሰጠች መሆኗን ገልጸዋል፡፡