አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በበጀት ዓመቱ ወደ ሥራ ለሚገቡ አዲስና በስራ ላይ ለሚገኙ ነባር ኢንተርፕራይዞች 4 ቢሊየን ብር ብድር እየተሰራጨ መሆኑን የክልሉ ሥራና ሥልጠና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የገበያ ልማትና ግብይት ዳይሬክተር ፍቅረማርያም የኔአባት እንደገለጹት፥ አዳዲስና ነባር ኢንተርፕራይዞች ውጤታማ እንዲሆኑ በቅንጅት እየተሰራ ነው።
ለዚህም ቢሮው ከፀደይ ባንክና ከዋልያ ዕቃ አቅራቢ የፋይናንስ ድርጅት ጋር ተቀናጅቶ ለኢንተርፕራይዞቹ የሚሆን ብድር ለማቅረብ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ከሚሰራጨው ብድር ውስጥም 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በተዘዋዋሪ፣ 1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ደግሞ በመደበኛ እንደሆነ አመልክተዋል።
ቀሪው 700 ሚሊየን ብር ብድር ደግሞ በዋልያ ዕቃ አቅራቢ ፋይናንስ ድርጅት አማካይነት እንደሚቀርብና ለማሽነሪ መግዣ እንደሚውል ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።
ብድሩን በማኑፋክቸሪንግ፣ በእንጨትና ብረታ ብረት፣ በባልትና ውጤቶች፣ በአልባሳትና ሌሎች አነስተኛ የሥራ ዘርፎች ለተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ሥር ለተደራጁ ከ62 ሺህ በላይ አንቀሳቃሾች እንደሚሰራጭ አመልክተዋል።
በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው ሩብ በመደበኛና ተዘዋዋሪ ብድር ከ215 ሚሊየን ብር በላይ ብድር ለተጠቃሚዎች መሰራጨቱን ገልጸዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።
እስካሁን ባለው በተዘዋዋሪ ብድር 127 ሚሊየን ብር የተሰራጨ ሲሆን፥ ገንዘቡ ለ702 የተዘዋዋሪ ብድር ተጠቃሚዎች እንዲደርስ ይደረጋልም ነው የተባለው።
በመደበኛው ደግሞ 88 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለማሰራጨት ተችሏል ብለዋል።
የብድር አቅርቦቱ አንቀሳቃሾች ያለባቸውን የገንዘብ ችግር በማቃለል ውጤታማ እንዳደረጋቸው ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!