ቢዝነስ

የነዳጅ ማደያ እስከ ጅቡቲ ድረስ በኦንላይን ሲስተም የሚያዝበት ስርዓት ይተገበራል- የነዳጅና ኢነርጅ ባለስልጣን

By Tamrat Bishaw

October 21, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከጥቅምት 13 ጀምሮ እያንዳንዱ የነዳጅ ማደያ ትዕዛዙን እስከ ጅቡቲ ድረስ በኦንላይን ሲስተም የሚያዝበት ስርዓት በአስገዳጅነት ይተገበራል ሲል የነዳጅና ኢነርጅ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የነዳጅና ኢነርጅ ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር በቀለች ኩማ ፤ ነዳጅን ለመቆጠብ የሚያስችሉ አሰራሮች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ከዚህ ውስጥም የነዳጅ ግብይቱን ዲጅታል ማድረግ እና ትዕዛዞችን በኦንላይን ሲስተም ብቻ ማድረግ ተጠቃሾች መሆናቸውን አንስተዋል።

በዚህም በአዲስ አበባ እና ሸገር ከተሞች ላይ የነዳጅ አቅርቦት ሠንሠለት አስተዳደር ስርዓት ከሐምሌ ወር ጀምሮ በአስገዳጅነት ሲተገበር መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

ከማክሰኞ ጥቅምት 13 ቀን 2016 ዓ/ም ጀምሮ ደግሞ የጸጥታ ችግር በሌለባቸው አካባቢዎች ላይ በሚገኙ ሁሉም ማደያዎች በአስገዳጅነት እንደሚተገበር ተናግረዋል።

የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ማደያዎች አገልግሎቱን ለማስጀመር ስልጠና መስጠት ስላልተቻለ ማደያዎች በነበረው ስርዓት እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል።

አሁን የሚተገበረው ስርዓት እያንዳንዱ የነዳጅ ማደያ ትዕዛዙን እስከ ጅቡቲ ድረስ በኦንላይን ሲስተም የሚያዝበት እንዲሁም ተቆጣጣሪው አካል (ባለሥልጣኑ) ሂደቱን እና ሁኔታውን የሚከታተልበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ቴክኖሎጂው የነዳጅ ሥርጭትና አጠቃቀምን ከጫፍ እስከ ጫፍ ለመቆጣጠር እንደሚያስችል ተነግሯል።

ይህ ስርዓት መተግበሩ እንደ ሀገር አለ አግባብ ሲወጡ የነበሩ ወጪዎችን የሚያስቀር እና ሕገወጥ አሰራርን ለመግታት የሚያስችል መሆኑን በቀለች ኩማ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ እና ሸገር ከተሞች ላይ እየተተገበረ በነበረበት ወቅት ሲያጋጥሙ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት ፤ ስርዓቱን ሙሉ በሙሉ ለመተግበር እና የሲስተም መቆራረጥ እንዳያጋጥም ከኢትዮቴሌኮም ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

በመሳፍንት እያዩ