የሀገር ውስጥ ዜና

የኦፓል ማዕድንን በጋራ ማልማት የሚያስችል ሥምምነት ተፈረመ

By Amele Demsew

October 20, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት እና የወሎ ዩኒቨርሲቲ የኦፓል ማዕድንን በጋራ ማልማት የሚያስችል የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱን የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጉታ ለገሠ (ዶ/ር) እና የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት መንገሻ አየነ (ዶ/ር) ተፈራርመዋል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ጉታ ለገሠ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንዳሉት÷ ማሰልጠኛ ተቋማትን በማቋቋምና የእሴት የማበልፀጊያ መድረኮችን በማመቻቸት ደረጃውን የጠበቀ የኦፓል ማዕድን ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ሥምምነቱ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ።

በሥምምነቱ መሰረት ለአራት አመት የሚቆይ ፕሮጀክት ተቀርጾ ተግባራዊ እንደሚደረግ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት መንገሻ አየነ (ዶ/ር በበኩላቸው ÷ሥምምነቱ የኦፓል ማዕድን ትርጉም ባለው ሁኔታ የአካባቢውንና የሀገር ኢኮኖሚን በሚጠቅም መልኩ ለማልማት ያስችላል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው በኦፓል ማዕድን ዙሪያ የተለያዩ ጥናቶችን ማከናወኑን ጠቁመው÷ ሥምምነቱ ከጥናት ባሻገር የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ የአመራረት ሂደቱን እና የገበያ ሁኔታ የሚያሻሽል እንደሆነ አስረድተዋል።