ዓለምአቀፋዊ ዜና

ግዙፍ ኅንፃዎችን በአነስተኛ ኃይል የሚያቀዘቅዝ ሥልት ያስተዋወቁት ተመራማሪ የሣይንስ ሽልማት አሸነፉ

By Alemayehu Geremew

October 21, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰማይ ጠቀስ ኅንፃዎችን በአነስተኛ ኃይል ማቀዝቀዝ የሚያስችል ሥልት የዘየዱት ተመራማሪ በሲንጋፖር ከፍተኛ ቦታ የሚሠጠውን የሣይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ሽልማት አሸነፉ፡፡

የ2023 የሀገሪቷን ፕሬዚዳንታዊ የሣይንስ እና ቴክኖሎጂ ሽልማት ያሸነፉት ቺው ቼንግ ዌይ (ዶ/ር) ÷ ሽልማቱን ያገኙት ‘በተርማል ኮንዳክሽን ሣይንሳዊ ሥልት’ አነስተኛ ኃይል በመጠቀም ሰማይ ጠቀስ ኅንፃዎችን ማቀዝቀዝ የሚያስችል ሥልት በማመላከታቸው ነው ተብሏል፡፡

በዛሬው ዕለት ሽልማቱን ያገኙት ቺው ቼንግ ዌይ (ዶ/ር) ÷የ42 ዓመት ጎልማሳ ሲሆኑ በሲንጋፖር ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ የንድፍ እና ምኅንድስና ኮሌጅ ተባባሪ ፕሮፌሰር እና ዲን መሆናቸውም ተጠቁሟል፡፡

በሲንጋፖር ‘የፕሬዚዳንቱ የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ሽልማት’ የላቀ የቴክኖሎጂ ግኝት ላበረከቱ ተመራማሪዎች እና መኀንዲሶች የሚሰጥ የሀገሪቱ ከፍተኛው የክብር ሽልማት መሆኑን ዘ ስትሬይትስ ታይምስ በፅሑፉ አስነብቧል፡፡

በተመራማሪው ግኝት መሠረት ግዙፍ ኅንፃዎች በሚገነቡበት ወቅት በኳንተም ሜካኒክስ ንድፈ ሐሳብ የሚሠሩ “ሙቀት አማቂ” ቁሶችን ከግንባታ ጠጠር እና ሲሚንቶ ጋር በመጠቀም የሰማይ ጠቀስ ኅንፃዎችን ሙቀት መቀነስ ይቻላል፡፡

ተመሳሳይ ሥልት ኅንፃው ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ክፍሎቹ ቀለም በሚቀቡበት ወቅት በመጠቀም የኅንፃውን ክፍሎች ለማቀዝቀዝ ማውጣት የሚያስፈልገውን የኃይል ሙቀት በእጅጉ መቀነስ ይቻላልም ነው የሚለው የተመራማሪው ግኝት፡፡