Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ከፓስፖርት የሙስና ተግባር ጋር ተያይዞ የተጠረጠሩ ደላሎችና የውጭ ዜጎች ፍርድ ቤት ቀረቡ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 9 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከፓስፖርት የሙስና ተግባር ጋር ተያይዞ የተጠረጠሩ ደላሎችና የውጭ ሀገር ዜጎችን ጨምሮ 10 ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀረቡ።

ዛሬ ከሰዓት ተጠርጣሪዎቹ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበው ጉዳያቸው ታይቷል።

በእነ አለሚቱ የኔአየው ዳኛቸው መዝገብ ከተካተቱ 10 ተጠርጣሪዎች መካከል ሁለት ደላሎች ሌሎች ሁለት በወንጀሉ ተሳትፈዋል የተባሉ የውጭ ሀገር ዜጎች ይገኙበታል።

ቀሪዎቹ ተጠርጣሪዎች ደግሞ የኢትዮጵያ ኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ አገልግሎት ሰራተኞች ናቸው።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዘርፍ መርማሪ በአስሩ ተጠርጣሪዎች ላይ የጥርጣሬ መነሻ ነጥቡን አቅርቧል።

በዚህም ተጠርጣሪዎቹ ከግለሰብና ከደላላ ጋር በጥቅም በመመሳጠር፣ ከህግ ውጪ ለውጭ ሀገር ዜጎች ከ10 ሺህ ብር እስከ 300 ሺህ ብር በሚደርስ ጉቦ በመቀበል ፓስፖርት በመስጠት እና በህጋዊ መንገድ የተመዘገቡ ተገልጋዮችን በማጉላላት በሀገር ጥቅም ላይ ጉዳት በማድረስ ሙስና ወንጀል መጠርጠራቸውን ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አብራርቷል።

ተጨማሪ ምርመራ ማጣሪያ ለማድረግና ማስረጃ ለመሰብሰብ የ14 ቀን ጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ችሎቱን ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው በደንበኞቻቸው ላይ ፖሊስ ያቀረበው የጥርጣሬ መነሻ ጊዜ ቀጠሮ ጥያቄን በመቃወም ተከራክረዋል።

ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ መሰጠት እንደሌለበት ገልጸው በመከራከር የደንበኞቻቸው የዋስትና መብት እንዲጠበቅ ጠይቀዋል።

ፖሊስ ደግሞ የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ በመቃወም ተከራክሯል።

የግራ ቀኝ ክርክሩን የመረመረው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ተጨማሪ የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ቀጠሮ መሰጠት እንደሚያስፈልግ በማመን የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ ለጊዜው በማለፍ የ14 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ቀጠሮ ለፖሊስ ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version