Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ለ2016/17 ምርት ዘመን 23 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዷል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለ2016/17 ምርት ዘመን 23 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በግዢ ለማቅረብ መታቀዱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ይሄም ካለፈው ዓመት 13 ነጥብ 9 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ አቅርቦት ጋር ሲነጻጸር የ9 ሚሊየን ኩንታል ጭማሪ እንዳለው ተመላክቷል፡፡

ባለፈው ዓመት አጋጥሞ የነበረው ዓይነት የግብዓት አቅርቦት ችግር እንዳይደገም ለማድረግም የግዥ ሂደቱን አስቀድሞ ለማከናወን የሚያስችል አዲስ መመሪያ ተግባር ላይ መዋሉ ተገልጿል፡፡

እስካሁንም የኤንፒኤስ ግብአት ካለፈው ዓመት በተሻለ ዋጋ ሙሉ በሙሉ መገዛቱም ተጠቁሟል።

የቀረውን የማዳበሪያ ግብዓት ዩሪያን ጨምሮ በተሻለ ዋጋ ለመግዛት እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ አመልክተዋል።

የኤንፒኤስ ማዳበሪያን ጨምሮ 13 ሚሊየን ኩንታል የተገዛ ሲሆን የማጓጓዝ ስራውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማከናወን ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ማዳበሪያ የጫነችው የመጀመሪያዋ መርከብ ከ10 ቀን በኋላ ጅቡት የምትደርስ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል ዘንድሮ ካለፈው ዓመት በዕጥፍ በመጨመር 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት በመስኖ ስንዴ ለማልማት መታቀዱን ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) አንስተዋል።

ተከስቶ የነበረው የአንበጣ መንጋ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር መዋሉም በመግለጫቸው ያነሱት የግብርና ሚኒስትሩ፤ በስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች የተከሰተውን የግሪሳ ወፍ ለመከላከል የመጀመሪያ ዙር ርጭት መካሄዱን ገልጸዋል።

ከነገ ጀምሮ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሁለተኛው ዙር የአውሮፕላን ርጭት እንደሚካሄድም ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በዝናብ እጥረት ምክንያት ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ላይም የስጋቱን ልክ በመለየት የሚደረገውን የድጋፍ ሁኔታ ለመወሰን እየተሰራ መሆኑ ተነስቷል፡፡

በይስማው አደራውና መሳፍንት እያዩ

Exit mobile version