Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በቂ እንቅልፍ የመተኛት የጤና በረከቶች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቂ እንቅልፍ ያለማግኘት ለብዙ በሽታዎች የመጋለጥ እድልን እንደሚጨምር በጤናው ዘርፍ የተጠኑ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡

በቂ እንቅልፍ መተኛት ማለት አልጋ ላይ የምናሳልፈው ጊዜ ማለት ሳይሆን በእንቅልፍ ያሳለፍነውን ጊዜ መጠን የሚገልጽ እንደሆነም ነው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚናገሩት፡፡

ጤናማ እንቅልፍ የሚለካው በእንቅልፍ ባሳለፍነው ጊዜ መጠን ፣ ያልተቆራረጠና ያልተረበሸ መሆኑና በዕለት ከዕለት የምንተኛበትን ሰዓት የጠበቀ መሆኑንም ነው ባለሙያዎች የሚገልጹት።

ሆኖም ግን የምንተኛበት ሰዓት እንደየ አኗኗር ዘይቤያችንና የስራችን ሁኔታ የሚለያይ በመሆኑ በየትኛውም ስዓት አዕምሯችን እረፍት ማግኘት በፈለገበት ሰዓት ማረፍ እና በቂ እንቅልፍ ማግኘት አስፈላጊ መሆኑንም ያነሳሉ፡፡

ስለሆነም በማንኛውም ሰዓት የደከመ ሰውነትን ለማሳረፍ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ እረፍት ማድረግና በቂ እንቅልፍ መተኛት ሰውነታችን ንቁና ጤናማ እንዲሆንና አዕምሯችንም ለፈጠራ ስራዎች እንዲነሳሳ፣ ለመማር ዝግጁ እንዲሆንና የማስታወስ ችሎታችን እንዲጨምር እንደሚያደርግ ይታመናል፡፡

አንጎል በእንቅልፍ ጊዜ መርዛማ ንጥረ ነገሮችን የማስወገጃ ሥርዓት እንዳለውና ይህም ለአልዛይመር ሊያጋልጠን የሚችልን ፕሮቲን እንደሚያስወግድና አንጎላችን እንደ አዲስ እንዲነቃቃ እንደሚያደርግ በርካታ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡

ከእንቅልፋችን ተኝተን ስንነሳ አብዛኛዎቹ የሰውነታችን ክፍሎች ውስጥ የሚካሄዱ ስርዓቶች ተነቃቅተው ስራቸውን በአግባቡ እንዲሰሩ እና እንዲታደሱ የማድረግ ኃይል ያለው ሲሆን በቂ እንቅልፍ ካላገኘን ግን ስርዓቱ እንደሚዛበም ነው የሚገልጹት፡፡

አንድ ሰው በቀን ስንት ሰአት መተኛት አለበት?

በቂ እንቅልፍ እንደየ እድሜ ደረጃው የሚለያይ ሲሆን እድሜያቸው እስከ አንድ አመት የሚሆኑ ጨቅላ ህጻናት በቀን ውስጥ ሸለብታን ጨምሮ ከ12 እስከ 16 ሰዓታት እንዲተኙ ይመከራል።

እንዲሁም እድሜያቸው ከአንድ ዓመት እስከ ሁለት ዓመት የሆናቸው ህጻናት በቀን ውስጥ ከ11 እስከ 14 ሰዓታት በቂ እንቅልፍ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል፡፡

እድሜያቸው ከሦስት እስከ አምስት ዓመት የሆናቸው ህጻናት ከ10 አስከ 13 ሰዓታት በቂ እንቅልፍ እንዲተኙ የሚመከር ሲሆን፥ ከስድስት እስከ 12 ዓመት እድሜ ውስጥ ያሉ ታዳጊዎች በቀን ውስጥ ከዘጠኝ ሰዓታት እስከ 12 ሰዓታት እንዲተኙ ይመከራል፡፡

በተጨማሪም ከ13 እስከ 18 ዓመት እድሜ ላይ ያሉ ታዳጊዎች ደግሞ ከስምንት እስከ 10 ሰዓታት እንዲተኙ የሚመከር ሲሆን፥ ከ18 አመት በላይ ያሉ አዋቂዎች ቢያንስ ሰባት ሰዓትና ከዚያ በላይ እንቅልፍ እንዲተኙ እንደሚመከር ከኤን አይ ኤች የጤና ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ፡፡

Exit mobile version