ቻይና የቤልት ኤንድ ሮድ ትብብርን በጥራት ለመተግበር ያስችለኛል ያለችውን ዕቅድ ይፋ አደረገች
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይና ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ የ”ቤልት ኤንድ ሮድ” ትብብርን በከፍተኛ ጥራት ለመተግበር ያስችላል ያሉትን የሀገሪቱን ዕቅድ ሥምንት ደረጃዎች ይፋ አደረጉ፡፡
ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ዕቅዱን ይፋ ያደረጉት በቤጂንጉ ሦስተኛው የ”ቤልት ኤንድ ሮድ” ዓለምአቀፍ የትብብር ፎረም የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ንግግር ባደረጉበት ወቅት መሆኑን ሲጂቲኤን ዘግቧል።
ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የቻይና ልማት ባንክ እና የቻይናው የወጪ – ገቢ ባንክ እያንዳንዳቸው 350 ቢሊየን ዩዋን (48 ነጥብ 75 ቢሊየን ዶላር) መድበው እንደሚንቀሳቀሱ ፕሬዚዳንት ሺ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም 80 ቢሊየን ዩዋን ለ”ሲልክ ኤንድ ሮድ” ፕሮጀክት ፈሰስ እንደሚደረግም አረጋግጠዋል፡፡
በፎረሙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ንግግር ያደረጉ ሲሆን የቻይና እና የአፍሪካ አኅጉር ታሪካዊ ግንኙነት እና ዕድገት ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡
የ”ቤልት ኤንድ ሮድ” ፎረምም የቻይና – አፍሪካን ትብብር በማጠናከር ረገድ መሠረት መጣሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አንስተዋል፡፡
የአፍሪካን ተፅዕኖ ፈጣሪነት እንደ “ቤልት ሮድ” ባሉ የባለ-ብዙ ወገን የትብብር ፎረሞች በመሳተፍ ማረጋገጥ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
የ”ቤልት ኤንድ ሮድ ትብብር” አውሮፓ እና እሲያን ከማስተሳሰር አልፎ አፍሪካን ፣ ላቲን አሜሪካን እንዲሁም ከ150 በላይ ሀገራትን እና 30 ዓለምአቀፍ ድርጅቶችን ያጣመረ ግዙፍ መርሐ-ግብር መሆን ችሏል፡፡
ሀገራቱና ድርጅቶቹም የትብብር የመግባቢያ ሠነድ ፈርመው ጥምረታቸውን አረጋግጠዋል፡፡