Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሀገር አቀፍ የሥራ አውደ-ርዕይ በሚሊኒየም አዳራሽ ተከፈተ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ከደረጃ ዶት ኮም እና ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ሀገር አቀፍ የሥራ አውደ-ርዕይ ተከፈተ።

አውደ-ርዕዩ አሠሪና ሠራተኛ የሚገናኙበትና በሚሊኒየም አዳራሽ የተዘጋጀ ሲሆን፥ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት እንደሚቆይ ተገልጿል፡፡

አውደ-ርዕዩን የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከፍተውታል።

በአውደ-ርዕዩ ላይ ከ23 ሺህ በላይ የሚሆኑ አዲስ ተመራቂዎች ከ200 በላይ ከሚሆኑ ከተለያየ ዘርፍ የተውጣጡ ቀጣሪ ድርጅቶች ይገናኙበታል ተብሏል።

አውደ ርዕዩ ተሳታፊ ተመራቂዎቹ ከቀጣሪዎቹ ጋር የሚተዋወቁበትና መረጃ የሚለዋወጡበት እንዲሁም የሥራ ዕድሎች የሚያገኙበት እንደሚሆንም ተጠቁሟል።

በአውደ ርዕዩ ሥራ ፈላጊዎች በቀጥታ ከቀጣሪዎች ጋር የሚገናኙበት መድረክ እንደተዘጋጀና በክፍት የሥራ ቦታዎች ምልመላ እንደሚደረግ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ለሥራ ፈላጊዎች እንዴት አቅማቸውን ማሳደግ እንደሚችሉ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክም እንዳለ ተገልጿል።

Exit mobile version