አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋዛ አል-አህሊ ባብቲስት ሆስፒታል በደረሰ ጥቃት ቢያንስ የ500 ንጹሐን ሕይወት ማለፉን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
እስራዔል በበኩሏ ጥቃቱ ወደ ግዛቷ ከሃማስ ወይም ከሂዝቦላህ የተወነጨፈ ሮኬት ኢላማውን ስቶ የተፈጸመ ነው በማለት ሁለቱ ታጣቂ ቡድኖች ሃላፊነቱን ይውሰዱ ስትል መረጃውን አጣጥላለች።
እንደ ሚኒስቴሩ መረጃ በጥቃቱ ሰለባ ከሆኑት በርካቶቹ ሴቶችና ሕፃናት ናቸው፡፡
በተመድ ድጋፍ የሚንቀሳቀስ አንድ ተፈናቃዮችን ያስጠለለ ትምህርት ቤትም የእስራዔል ጥቃት ሰለባ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የዓለም መንግስታት በተለይ በጋዛ ሆስፒታል ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ተቃውሟቸውን ማሰማት ጀምረዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረስ እችል ዘንድ በአስቸኳይ ጦርነት ይቁም ሲል አሳስቧል፡፡
የተቃውሞ ሰልፎች በመካከለኛው ምሥራቅና በሌሎችም አካባቢዎች እየተስተዋሉ መሆኑንም አልጀዚራ እና አር ቲ በዘገባቸው አስነብብዋል።
እስራኤል የጋዛን ሆስፒታል በቦንብ መደብደቧን ተከትሎም በጆርዳን ሊካሄድ የነበረው እስራኤል እና ፍልስጤምን በአሜሪካ እና ግብፅ ለማሸማገል የተያዘው ዕቅድ መሰረዙ ታውቋል።
የጆርዳኑ መሪ ሞሐመድ አባስ ገና ጥቃቱን ሲሰሙ ከስብሰባው መልቀቃቸው ተነግሯል፡፡
የእስራዔል እና ፍልስጤም ጦርነት ከጀመረበት ከፈረንጆቹ ጥቅምት 7 ጀምሮ እስካሁን ከሁለቱ ወገን 4 ሺህ 500 የሚጠጉ ንጹሃን ሕይወታቸውን ማጣታቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡