Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሀገራት የሳይበር ወንጀሎችን ለመከላከል በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ተመለከተ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራት የሳይበር ወንጀሎችን ለመከላከል የተቀናጀ አሰራር መከተል እንደሚገባቸው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ ገለጹ፡፡

በዩናይትድ አረብ ኢሚሬቶች ዱባይ ጂይቴክስ ግሎባል “የሳይበር ጥቃት አለም አቀፍ ኪሳራ” በሚል ርዕስ የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡

አቶ ሰለሞን ሶካ በፓናል ውይይቱ ላይ እንደገለጹት÷ የሳይበር ወንጀሎች በተቋማት ላይ ከሚያደርሱት ከፍተኛ የገንዘብ ኪሳራን በተጨማሪ ተቋማቱን የህዝብ አመኔታ ሊያሳጣቸው ይችላል፡፡

በተጨማሪም÷ የሳይበር ምህዳሩን በመጠቀም የሚሰነዘሩ የስነ-ልቦና ጦርነት ሀገራትን ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሀገራት ከዚህ ከባድ ኪሳራ ለመላቀቅ ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የሳይበር ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ ተቋማት ከሳይበር ወንጀል ጋር ተያይዘው የሚመጡ አደጋዎችን ለመቀነስ ሰውን ያማከለ አካሄድ መከተል እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያን የሳይበር ጥቃት የመከላከል ተሞክሮ በመድረኩ ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ እንደ ሀገር ጥቃቶችን መከላከል የሚያስችሉ አዋጆችን፣ ደንቦችናና ሌሎች የፖሊሲ አማራጮችን እየተተገበረ መሆኑን ጠቁመዋል።

ተለዋዋጭ በሆነዉ የሳይበር ምህዳር ውስጥ ተቋማትና ግለሰቦች ከምህዳሩ አዳዲስ አዝማሚያዎች ጋር በማጣጣም ሊደርስባቸዉ የሚችልን ሁሉን አቀፍ ኪሳራ መቀነስ ይገባልም ነው ያሉት፡፡

እንደ ሀገር ከጊዜዉ ጋር አብረዉ በሚሄዱ ዘርፎች ላይ ጥናትና ምርምርን በማድረግ ሊከሰቱ የሚችሉ ስጋቶች ላይ እየተሰራ እንደሆነም መጠቆማቸውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር መረጃ ያመላክታል።

Exit mobile version