የሀገር ውስጥ ዜና

ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) ከቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ያደረጉት ምክክር ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ ያላትን ፍላጎት ያሳየ ነው – ቢልለኔ ስዩም

By Alemayehu Geremew

October 16, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ ጋር ያደረጉት ምክክር ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ ያላትን ፍላጎት ያሳየችበት መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እና የልዑክ ቡድናቸው በቻይና እያደረጉ የሚገኙትን ይፋዊ የስራ ጉብኝት አስመልክቶ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም÷የቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋዊ አቀባበል ማድረጋቸውንና የአቀባበል ሥነ-ሥርዓቱ የሁለቱን ሀገራት ጠንካራ ግንኙነት በሚያመላክት መልኩ መከናወኑን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የሁለትዮሽ ግንኙነት ለዘመናት የዘለቀ እና ጠንካራ እንደሆነ መግለጻቸውን አንስተዋል፡፡

አሁንም የሁለትዮሽ ግንኙነቱን የበለጠ ከፍ ለማድረግ ፍላጎት መኖሩን መጥቀሳቸውን አመላክተዋል።

በውይይታቸው ወቅትም መሪዎቹ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የምጣኔ ሃብት ትብብር ግንኙነት ማጠናከሪያ መንገዶችን ማንሳታቸውን ገልጸዋል።

ከውይይቱ በኋላም ሁለቱ መሪዎች በተገኙበት በሀገራቱ መካከል 14 የሚሆኑ የተለያዩ የመግባቢያ ስምምነቶች መፈረማቸውንም አብራርተዋል።