Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በቡና ልማት የተሰማሩ ሴቶች የተሳተፉበት ዓለም አቀፍ ጉባዔ በመዲናዋ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ33 ሀገራት የተውጣጡ በቡና ልማት የተሰማሩ ሴቶች የተሳተፉበት ዓለም አቀፍ ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

የጉባኤው አላማ በቡና ልማት ዘርፍ የተሰማሩ ሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና በዘርፉ የሚገጥማቸውን ችግሮች መፍታት የሚያስችሉ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በፖሊሲና በአሠራር አካተው እንዲሰሩ ማመላከት ነው ተብሏል፡፡

በጉባዔው በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ33 ሀገራት የተውጣጡ በዘርፉ እሴት ሠንሰለት የተሰማሩ ሴቶች፣ ቡና ገዥዎችና በዘርፉ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በጉባዔው ታድመዋል።

በመድረኩ በዘርፉ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚረዱ የመፍትሔ ሃሳቦች የሚያመላክቱ የጥናት ውጤቶች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ኢትዮጵያ በቡናው መስክ ያላትን እምቅ አቅም የማስተዋወቅ መርኃ-ግብሮች እንደሚካሄዱም መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ጉባዔው ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን÷ ተሳታፊዎች በተመረጡ ቡና አብቃይ አካባቢዎችን ይጎበኛሉ ተብሏል።

Exit mobile version