የሀገር ውስጥ ዜና

የሰንደቅ አላማ ቀን በተለያዩ ሀገራት በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ተከበረ

By Amele Demsew

October 16, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 16ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በተለያዩ ሀገራት በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽ/ቤቶች ተከብሯል፡፡

የሰንደቅ አላማ ቀን በሕንድ፣ ጃፓን ፣ኳታር፣ ጣሊያን፣ ታንዛንያ ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ጂቡቲ፣ በተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች እና ሌሎች ሀገራት በሚገኙ ኤምባሲዎች በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል፡፡

በህንድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በተከበረው የሰንደቅ ላማ ቀን ላይ አምባሳደር ደመቀ አጥናፉን ጨምሮ ሌሎች ዲፕሎማቶች እና የኤምባሲው ሰራተኞች ተገኝተዋል፡፡

አምባሳደር ደመቀ ÷ሰንደቅ ዓላማ የአንድነትና የነፃነትና ምልክት በመሆኑ ቀኑ አካታች ሁለንተናዊ ዕድገትን ለማስመዝገብና የሀገር ውስጥ ኢኮኖሚ ዕቅዱን በተሟላ ሁኔታ ለማሳካት ቃልኪዳናችን የምናድስበት ነው ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ÷የሰንደቅ ዓለማ ቀን በቤይሩት ኢፌዴሪ ቆንስላ ጄ/ጽ/ቤት፣ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ሚሲዮን እና በተለያዩ ሀገራት በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽ/ቤቶች በተለያዩ ሥነ-ሥርዓቶች ተከብሯል፡፡

ባዕሉ ሲከበር ሀገራዊ አንድነትን እና ሕብረ ብሔራዊ መግባባትን ለማጠናከር ሁሉም ቃል መግባት እንዳለበት መገለጹንም ከኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽ/ቤቶች ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡