የሀገር ውስጥ ዜና

በሀውዜን በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ12ኛ ክፍል ፈተና የወሰዱ 6 ተማሪዎች ህይወት አለፈ

By Amele Demsew

October 14, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል ሀውዜን ከተማ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ 6 ተማሪዎች ሕይወት አለፈ።

አደጋው ተማሪዎች ከዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ የ12ኛ መልቂያ ፈተናን ተፈትነው ትናንት ከሰዓት በኋላ ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲጓዙበት የነበረ አውቶቡስ በመገልበጡ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በአደጋውም እስካሁን የስድስት ተማሪዎች ሕይወት ማለፉን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳዳር ት/ቢሮ ሃላፊ ኪሮስ ግዑሽ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

በተጨማሪም 24 ተማሪዎች ላይ ከባድ እና ከ20 በላይ ተማሪዎች ላይ ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን ጠቁመዋል።

ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች በአይደር ሆስፒታል እንዲሁም ቀላልጉዳት ያጋጠማቸውም በሀውዜን ጤና ተቋማት ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የአደጋውን መንስኤ ፖሊስ እያጣራ መሆኑንም ኃላፊው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል።

ኪሮስ ግዑሽ (ዶ/ር) በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ ተማሪዎች ቤተሰቦች እና ወዳጅ ዘመዶች መጽናናትን ተመኝተዋል።

በመላኩ ገድፍ