Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በክልላችን 639 ሺህ 105 ሄክታር መሬት ላይ የማሽላ ሰብል ለምቷል – ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በምርት ዘመኑ 464 ሺህ 821 ሄክታር መሬት ላይ የማሽላ ሰብል ለማልማት ታቅዶ ከእቅድ በላይ 639 ሺህ 105 ሄክታር መሬት መልማቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ያለፈው ዓመት በብዙ ስኬቶችና ተሞክሮዎች የታጀበ ነበር ብለዋል።

የስኬቱ ቁልፍ ፖለቲካ ቁርጠኝነት፣ የህዝብ ተሳትፎና በሳይንሳዊ እውቀት የታገዘ ጠንካራ ስራ መሆኑን ገልጸው፤ ወደዚህኛው ዓመት ስንሻገርም ባዶ እጃችንን አልነበረም፤ ከጅምር ስኬቶቻችን በተጨማሪ ፈተናዎችን ተጋፍጦ ስኬት ማስመዝገብ እንደሚቻል በቂ ተሞከሮ ጨብጠን ነው ብለዋል።

እነዚህ መደላድሎች በሁሉም ዘርፎች የበለጠ ለመስራት እንደሚያነሳሱ ጠቅሰው፤ በግብርና ዘርፍ ስኬት እየተመዘገበና ጅምሩን ማጠናከር ሁኔታ መታየቱን አመልክተዋል።

እንደ ሀገር ለማሳካት ካቀድነው ሁለንተናዊ ብልጽግና ለመድረስ የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ አሁን ካለበት መልካም ጅማሮ የበለጠ ማዘመን ግድ የሚለን ጉዳይ መሆኑን ሁሉም መገንዘብ አለበት ሲሉም ገልጸዋል።

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተተገበሩ ካሉ የኢኒሼቲቭ ሰብሎች አንዱ ማሽላ መሆኑን በመግለጽ፤ በክልሉ መንግስት የዝናብ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ድርቅን በመቋቋም ከፍተኛ ምርት የሚሰጥ የማሽላ ዝርያ በማስፋፋት ላይ እንደሆነ አመልክተዋል።

በዚህም በተለያዩ የኦሮሚያ ቆላማ አካባቢዎች ላይ የሚገኙ አርብቶ አደሮችን በኩታ ገጠም በማደራጀ ከፍተኛ የማሽላ እርሻ እንዲለማ እያገዘ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በክልላችን በአመቱ 464 ሺህ 821 ሄክታር መሬት በማሽላ ለማልማት ታቅዶ ከእቅድ በላይ 639 ሺህ 105 ሄክታር መሬት ለምቷል በማለት ጠቅሰው፤ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ባቢሌ ወረዳ እየለማ የሚገኘው የማሽላ እርሻም በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል ብለዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version