አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዳውሮ ዞን ተርጫ አጠቃላይ ሆስፒታል ከአንዲት የ65 ዓመት ዕድሜ ካላቸው እናት 11 ኪሎግራም የሚመዝን ዕጢ በተሳካ ቀዶ ህክምና መውጣቱን ሆስፒታሉ አስታወቀ።
በሆስፒታሉ የማህጸንና ጽንስ ስፔሻሊስት ዶክተር ወንድማገኝ ሲሳይ÷ አዛውንቷ ለአምስት ዓመታት ህክምና ሲከታተሉ መቆየታቸውን ተናግረው ከአንድ ወር በፊት በምርመራ ተረጋግጦ ዛሬ ጠዋት በተሳካ ሁኔታ መውጣት ችሏል ብለዋል።
ቀዶ ህክምናው 2 ሰዓት ከ30 ደቂቃ የፈጀ ሲሆን አምስት የህክምና ባለሙያዎች መሳተፋቸውን ዶክተር ወንድማገኝ ጠቅሰዋል።
የቀዶ ህክምና የተደረገላቸው እናት አሁን ላይ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙም መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ይህን የሚያክል ዕጢ በብዛት የተለመደ አለመሆኑን ጠቅሰው መጠኑ ከፍ ያለ ዕጢ የህክምና ሥራን የሚያወሳስብ መሆኑን አብራርተዋል።