የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ እየተተገበረ ያለው የት/ቤቶች የምገባ መርሐ-ግብር በዓለም አቀፍ ተቋማት ተጎበኘ

By Alemayehu Geremew

October 13, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች እየተተገበረ የሚገኘው የተማሪዎች የምገባ መርሐ- ግብር በዓለም አቀፍ ተቋማት ተጎብኝቷል፡፡

በደጃዝማች ወንድይራድ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት በተካሄደው ጉብኝት÷ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ መርችዋክስ፣ የፊላንድ ሚሽን ምክትል ዳይሬክተር ላራ ኔልቶናን፣ በዓለም አቀፉ የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ክሪስ ሪኮይ፣ በድርጅቱ የኢትዮጵያ የትምህርት ቤት ምገባ ዳይሬክተር ሃና ፒተርሰን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።

አምባሳደር ሬሚ መርችዋክስ በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት÷ በአዲስ አበባ እየተተገበረ ያለው የትምህርት ቤት ምገባ መርሐ-ግብር ለሌሎች ተሞክሮ መሆን የሚችል ነው፡፡

መርሐ-ግብሩ በተማሪዎች ውጤት መሻሻል ላይ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማበርከቱም ተገልጿል፡፡

በአዲስ አበባ ተግባራዊ የሆነው የምገባ መርሐ- ግብር በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ማግኘቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡

በመዲናዋ የከተማ ግብርናን በመተግበር ለምገባ መርሐ- ግብሩ የሚውሉ ግብዓቶችን ማቅረብ መቻሉም ተመላክቷል፡፡