የሀገር ውስጥ ዜና

በጋምቤላ ክልል የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን በበጀት ዓመቱ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው ተባለ

By Alemayehu Geremew

October 13, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል የተጓተቱ ነባር ፕሮጀክቶችን በበጀት ዓመቱ ለማጠናቀቅ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ እንደሚገኝ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ።

የክልሉ ካቢኔ አባላትና የሚመለከታቸው አካላት በክልሉ የግንባታ ፕሮጀክቶች ዕቅድ አፈፃፀም ዙሪያ መወያየታቸውን የክልሉ ፕሬስ ሴክሬተሪያት መረጃ ያመለክታል፡፡

አቶ ኡሞድ ኡጁሉ÷ በክልሉ በመገንባት ላይ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብለዋል።

በግንባታ ያሉ ፕሮጀክቶች በአፈጻጸም ሂደት የሚገጥማቸዉን ማነቆዎች በመለየት አሥፈላጊዉ ድጋፍና ክትትል ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት አሥፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተንኩዌይ ጆክ በበኩላቸው÷ ፕሮጀክቶቹ በ2007 የተጀመሩ ቢሆንም በበጀት ውስንነትና በተለያዩ ምክንያቶች ተጓትተው መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት እንዲጠናቀቁም የክልሉ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በጀት ተመድቦ እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።