አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የ104 ዓመቷ አዛውንት በከፍተኛ ዝላይ ስማቸውን በዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ካስመዘገቡ ከቀናት በኋላ ህይወታቸው ማለፉ ተሰምቷል።
በአሜሪካ ቺካጎ ግዛት ነዋሪ የሆኑት የ104 ዓመቷ ዶሮቲ ሆፍነር በቅርቡ በዕድሜ ትልቋ ከአውሮፕላን በፓራሹት የዘለሉ በሚል በዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ (ጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ) የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡
የሆፍነር የቅርብ ጓደኛቸው ጆ ኮናንት አዛውንቷ ሰኞ ጠዋት በብሩክዴል ሐይቅ ዳርቻ በሚገኘው የአረጋውያን መጠለያ በተኙበት ህይወታቸው አልፎ መገኘቱን ተናግረዋል።
አዛውንቷ ቀልጣፋ፣ ንቁ፣ ብርቱ እና እዕምሯቸውም የሰላ እንደነበር በማዕከሉ በአረጋውያን ተንከባካቢነት ሥራ ላይ የሚገኙት ጓደኛቸው መናገራቸውን ኤ ቢ ሲ ኒውስ ዘግቧል፡፡
የ104 ዓመቷ ሆፍነር በፈረንጆቹ ጥቅምት 1 ቀን ከ13 ሺህ ጫማ ወይም ከ4 ሺህ 100 ሜትር ከፍታ ከአውሮፕላን ላይ በፓራሹት በመዝለል በዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ስማቸውን ማስፈር ችለዋል፡፡11:27